2 በገል በር መግቢያ አጠገብ ወዳለው ወደ ሄኖም ልጅ ሸለቆ ውጣ። በዚያም የምነግርህን ቃል ተናገር፤
3 እንዲህም በል፤ ‘የይሁዳ ነገሥታትና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ለሰሚው ሁሉ ጆሮ የሚዘገንን ክፉ ነገር እነሆ በዚህ ስፍራ አመጣለሁ፤
4 እኔን ትተውኝ፣ ይህን ስፍራ የባዕድ አማልክት ቦታ አድርገውታልና። እነርሱም ሆኑ አባቶቻቸው፣ የይሁዳ ነገሥታትም ለማያውቋቸው አማልክት ሠውተዋል፤ ይህንም ስፍራ በንጹሓን ደም ሞልተውታል፤
5 እኔም ያላዘዝኋቸውን፣ ያልተናገርኋቸውን፣ ፈጽሞም ያላሰብሁትን፣ ወንዶች ልጆቻቸውን በእሳት ሊሠውለት ለበኣል መስገጃ ኰረብታዎች ሠርተዋል።
6 ስለዚህ ሰዎች ይህን ስፍራ የዕርድ ሸለቆ እንጂ ከእንግዲህ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ብለው የማይጠሩበት ዘመን ይመጣል፤ ይላል እግዚአብሔር።
7 “ ‘በዚህ ስፍራ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ዕቅድ አፈርሳለሁ፤ በጠላቶቻቸው ፊት ሕይወታቸውን በሚሹት እጅ በሰይፍ እንዲወድቁ አደርጋለሁ፤ ሬሳቸውንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ምግብ አድርጌ እሰጣለሁ።
8 ይህችን ከተማ ድምጥማጧን አጠፋለሁ፤ ለመሣለቂያም አደርጋታለሁ፤ በዚያም የሚያልፉ ሁሉ ከደረሰባት ጒዳት የተነሣ ወይ ጒድ! ይላሉ ያሾፋሉም።