1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ወደ ይሁዳ ንጉሥ ቤተ መንግሥት ውረድ፤ ይህንም መልእክት በዚያ እንዲህ ብለህ ተናገር፤
2 ‘በዳዊት ዙፋን የተቀመጥህ፣ የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፤ አንተና መኳንንትህ፣ በእነዚህም በሮች የሚገባ ሕዝብህ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
3 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ፍትሕንና ጽድቅን አድርጉ፤ የተበዘበዘውን ከጨቋኙ እጅ አድኑት፤ መጻተኛውን፣ ወላጅ የሌለውንና መበለቲቱን አትበድሉ፤ አትግፏቸውም፤ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደም አታፍስሱ።
4 እነዚህን ትእዛዛት በሚገባ ብትጠብቁ፣ በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታት፣ ከመኳንንታቸውና ከሕዝባቸው ጋር በሠረገሎችና በፈረሶች ተቀምጠው በዚህ ቤተ መንግሥት በሮች ይገባሉ፤ ይወጣሉም።
5 ነገር ግን እነዚህን ትእዛዛት ባትጠብቁ፣ ይህ ቤተ መንግሥት እንዲወድም በራሴ ምያለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር።’ ”