ኤርምያስ 22:2-8 NASV

2 ‘በዳዊት ዙፋን የተቀመጥህ፣ የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፤ አንተና መኳንንትህ፣ በእነዚህም በሮች የሚገባ ሕዝብህ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።

3 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ፍትሕንና ጽድቅን አድርጉ፤ የተበዘበዘውን ከጨቋኙ እጅ አድኑት፤ መጻተኛውን፣ ወላጅ የሌለውንና መበለቲቱን አትበድሉ፤ አትግፏቸውም፤ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደም አታፍስሱ።

4 እነዚህን ትእዛዛት በሚገባ ብትጠብቁ፣ በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታት፣ ከመኳንንታቸውና ከሕዝባቸው ጋር በሠረገሎችና በፈረሶች ተቀምጠው በዚህ ቤተ መንግሥት በሮች ይገባሉ፤ ይወጣሉም።

5 ነገር ግን እነዚህን ትእዛዛት ባትጠብቁ፣ ይህ ቤተ መንግሥት እንዲወድም በራሴ ምያለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር።’ ”

6 ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ይሁዳ ንጉሥ ቤተ መንግሥት እንዲህ ይላል፤“አንተ ለእኔ እንደ ገለዓድ፣እንደ ሊባኖስ ተራራ ጫፍ ውብ ብትሆንም፣በርግጥ እንደ ምድረ በዳ፣ሰው እንደማይኖርባቸው ከተሞች አደርግሃለሁ።

7 በነፍስ ወከፍ መሣሪያ የሚይዙትን፣አጥፊዎችን በአንተ ላይ አዘጋጃለሁ።ምርጥ የዝግባ ዛፎችን ይቈርጣሉ፤ወደ እሳትም ይጥሏቸዋል።

8 “ከተለያየ አገር የመጡ ሕዝቦች በዚህች ከተማ በኩል ሲያልፉ፣ ‘እግዚአብሔር በዚህች ታላቅ ከተማ ላይ ለምን እንዲህ አደረገ?’ እያሉ እርስ በርስ ይነጋገራሉ፤