ኤርምያስ 32:20-26 NASV

20 በግብፅ ታምራትንና ድንቆችን አደረግህ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በእስራኤልና በሰው ልጆች ሁሉ መካከል እንደዚያው እያደረግህ ዛሬም ስምህ ገናና ነው።

21 በታምራትና በድንቅ፣ በብርቱ እጅና በተዘረጋች ክንድ፣ እጅግ በሚያስፈራም ግርማ ሕዝብህን እስራኤልን ከግብፅ አወጣህ።

22 ለአባቶቻችን ልትሰጣቸው የማልህላቸውን፣ ማርና ወተት የምታፈሰውን ይህችን ምድር ሰጠሃቸው፤

23 ወደዚያም ገብተው ወረሷት፤ ነገር ግን አልታዘዙህም፤ ሕግህንም አልጠበቁም፤ እንዲያደርጉት ያዘዝሃቸውን ከቶ አላደረጉም፤ ስለዚህ ይህን ሁሉ ጥፋት በላያቸው አመጣህ።

24 “እነሆ፤ ከተማዪቱን ለመያዝ የዐፈር ድልድል በዙሪያዋ ተሠርቶአል፤ ከሰይፍ፣ ከራብና ከቸነፈር የተነሣ ከተማዪቱን ለሚወጓት ለባቢሎናውያን ዐልፋ ልትሰጥ ነው፤ እንደምታየውም የተናገርኸው እየተፈጸመ ነው።

25 አንተ ግን ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከተማዪቱ ለባቢሎናውያን አልፋ እየተሰጠች፣ ‘መሬቱን በብር ግዛ፤ ግዢውንም በምስክሮች ፊት ፈጽም’ ትለኛለህ።”

26 ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤