ኤርምያስ 32:35-41 NASV

35 ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለሞሎክ ይሠው ዘንድ በሄኖም ሸለቆ ለበኣል መስገጃ ኰረብቶችን ሠሩ፤ ነገር ግን ይሁዳን ኀጢአት ለማሠራት እንደዚህ ያለውን አስጸያፊ ተግባር እንዲፈጽሙ እኔ አላዘዝሁም፤ ከቶም አላሰብሁም።

36 “ ‘በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር ለባቢሎን ንጉሥ ዐልፋ ትሰጣለች’ ስላልሃት ስለዚህች ከተማ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

37 “በጽኑ ቍጣዬና በታላቅ መቅሠፍቴ እነርሱን ካሳደድሁበት ምድር ሁሉ በእውነት እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደዚህም ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፤ በሰላምም እንዲቀመጡ አደርጋቸዋለሁ።

38 እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።

39 ለእነርሱና ከእነርሱም በኋላ ለልጆቻቸው መልካም እንዲሆንላቸው ዘወትር ይፈሩኝ ዘንድ፣ አንድ ልብ አንድም ሐሳብ እሰጣቸዋለሁ።

40 መልካምን ነገር ለእነርሱ ከማድረግ እንዳልቈ ጠብና ከእኔም ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በውስጣቸው ላኖር ከእነርሱ ጋር የዘላለም ቃል ኪዳን እገባለሁ።

41 ለእነርሱ መልካም በማድረግ ደስ ይለኛል፤ በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴ በእውነት በዚህች ምድር እተክላቸዋለሁ።’ ”