5 ሴዴቅያስንም ወደ ባቢሎን ይወስደዋል፤ በፍርዴ እስከምጐበኘውም ድረስ በዚያ ይቈያል፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ከባቢሎናውያን ጋር ብትዋጉ አይሳካላችሁም” ይላል’ ትላለህ።”
6 ኤርምያስም የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ አለ፦
7 “የአጎትህ የሰሎም ልጅ አናምኤል ወደ አንተ መጥቶ፣ ‘የመቤዠት መብት የአንተ ስለ ሆነ፣ በዓናቶት ያለውን መሬቴን ግዛኝ’ ይልሃል።”
8 እግዚአብሔርም እንደ ተናገረኝ፣ የአጎቴ ልጅ አናምኤል ወደ ዘብ ጠባቂዎቹ አደባባይ መጥቶ፣ “የመቤዠቱን ርስት የማድረጉ መብት የአንተ ስለ ሆነ፣ በብንያም አገር በዓናቶት ያለውን መሬቴን ለራስህ እንዲሆን ግዛው” አለኝ። ይህም የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ ዐወቅሁ፤
9 ስለዚህ በዓናቶት ያለውን መሬት ከአጎቴ ልጅ ከአናምኤል ገዛሁ፤ ዐሥራ ሰባት ሰቅል ብር መዝኜ ሰጠሁት።
10 በውሉም ሰነድ ላይ ፈረምሁ፤ አሸግሁትም። ብሩንም በምስክሮች ፊት በሚዛን መዘንሁለት።
11 የስምምነቱ ዝርዝር ያለበትን፣ የታሸገውንና ያልታሸገውን የግዢውን የውል ሰነድ ወሰድሁ፤