ኤርምያስ 34:3-9 NASV

3 አንተም በእርግጥ ትያዛለህ ዐልፈህም ለእርሱ ትሰጣለህ እንጂ ከእጁ አታመልጥም። የባቢሎንን ንጉሥ በዐይኖችህ ታየዋለህ፤ ፊት ለፊትም ያነጋግርሃል፤ ወደ ባቢሎንም ትሄዳለህ።

4 “ ‘ነገር ግን፣ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር ስለ አንተ እንዲህ ይላል፤ በሰይፍ አትሞትም፤

5 በሰላም ትሞታለህ። ሕዝቡ ከአንተ በፊት ለነበሩት ነገሥታት አባቶችህ ክብር በቀብራቸው ጊዜ እሳት እንዳነደዱ፣ በቀብርህም ጊዜ ስለ ክብርህ እሳት ያነዳሉ፤ “ዋይ ዋይ ጌታችን!” እያሉም ያለቅሱልሃል፤ እኔ ራሴ ይህን ቃል ተናግሬአለሁና፤ ይላል እግዚአብሔር።’ ”

6 ነቢዩ ኤርምያስ ይህን ሁሉ ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስ በኢየሩሳሌም ነገረው፤

7 በዚህም ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ሰራዊት ኢየሩሳሌምንና የቀሩትን የይሁዳ ከተሞች ለኪሶንና ዓዜቃን እየወጋ ነበር፤ ከተመሸጉት የይሁዳ ከተሞችም የቀሩት እነዚሁ ብቻ ነበሩና።

8 ንጉሡ ሴዴቅያስ ባሪያዎችን ነጻ ለማውጣት ከኢየሩሳሌም ሕዝብ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን ካደረገ በኋላ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ።

9 እያንዳንዱ ሰው፣ ዕብራዊ የሆነውን ወንድ ባሪያውንና ዕብራዊት የሆነችውን ሴት ባሪያውን ነጻ ማውጣት ነበረበት፤ ማንም ሰው አይሁዳዊ ወንድሙን በባርነት መግዛት አልነበረበትም።