ኤርምያስ 35:13-19 NASV

13 “የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሂድ፤ ለይሁዳ ሰዎችና ለኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ቃሌን ትጠብቁ ዘንድ ከዚህ አትማሩምን?’ ይላል እግዚአብሔር፤

14 ‘የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ ልጆቹ የወይን ጠጅ እንዳይጠጡ አዘዛቸው፤ ይህም ትእዛዝ ተጠብቆአል፤ የአባታቸውን ትእዛዝ ስለ ጠበቁ እስከ ዛሬ ድረስ የወይን ጠጅ አይጠጡም፤ እናንተ ግን እኔ ደጋግሜ ብናገራችሁም፤ አልታዘዛችሁኝም።

15 አገልጋዮቼን ነቢያትን ሁሉ ደጋግሜ ወደ እናንተ ላክሁ፤ እነርሱም፣ “እያንዳንዳችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ምግባራችሁን አስተካክሉ፤ ለእናንተና ለአባቶቻችሁ በሰጠኋቸው ምድር ትኖሩ ዘንድ ሌሎቹን አማልክት ለማገልገል አትከተሉ” አልኋችሁ። እናንተ ግን ጆሮአችሁን ወደ እኔ አላዘነበላችሁም፤ አልሰማችሁኝምም።

16 የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብ ዘሮች አባታቸው የሰጣቸውን ትእዛዝ ጠብቀዋል፤ ይህ ሕዝብ ግን አልታዘዘኝም።’

17 “ስለዚህ የእስራኤል አምላክ፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እነሆ፤ በይሁዳና በኢየሩሳሌም በሚኖሩት ሁሉ ላይ አደርሳለሁ ያልሁትን ጥፋት ሁሉ አመጣባቸዋለሁ፤ በተናገርኋቸው ጊዜ፣ አልሰሙኝምና በጠራኋቸውም ጊዜ አልመለሱልኝም።’ ”

18 ኤርምያስም ሬካባውያንን እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የአባታችሁን የኢዮናዳብን ትእዛዝ ስለ ጠበቃችሁ፤ መመሪያውን ስለ ተከተላችሁ፤ ያዘዛችሁንም ሁሉ ስለ ፈጸማችሁ’

19 የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ከሬካብ ልጅ ከኢዮናዳብ ወገን የሚያገለግለኝ ሰው ለዘላለም አይታጣም።’ ”