ኤርምያስ 41:6-12 NASV

6 የናታንያ ልጅ እስማኤል ሊገናኛቸው እያለቀሰ ከምጽጳ ወጣ፣ ሲያገኛቸውም፣ “ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ ኑቃ አላቸው።

7 ወደ ከተማዪቱ በገቡ ጊዜ፣ የናታንያ ልጅ እስማኤልና አብረውት የነበሩ ሰዎች ዐረዷቸው፤ በውሃ ማጠራቀሚያ ጒድጓድ ውስጥም ጣሏቸው።

8 ከተገደሉት ጋር የነበሩ ዐሥር ሰዎች ግን እስማኤልን፣ “እባክህ አትግደለን! በዕርሻችን ውስጥ የሸሸግነው ስንዴና ገብስ፣ የወይራ ዘይትና ማር ስላለን እባክህን አትግደለን” አሉት። እርሱም ተዋቸው፤ ከሌሎቹም ጋር አልገደላቸውም።

9 እስማኤል ከጎዶልያስ በተጨማሪ የገደላቸው ሰዎች ሁሉ ሬሳ የተጣለበት የውሃ ማጠራቀሚያ ጒድጓድ ንጉሡ አሳ የእስራኤልን ንጉሥ ባኦስን ስለ ፈራ ለመከላከል ያሠራው ነበር፤ ይህን ጒድጓድ፤ የናታንያ ልጅ እስማኤል በሬሳ ሞላው።

10 እስማኤል በምጽጳ የቀረውን ሕዝብ ሁሉ ምርኮኛ አደረገ፤ እነርሱም የባቢሎን የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡረዘረዳን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በላያቸው ገዥ አድርጎ የሾመባቸው የንጉሡ ሴቶች ልጆችና በዚያ የቀሩት ሌሎች ሰዎች ሁሉ ነበሩ። የናታንያ ልጅ እስማኤል እነዚህን ማርኮ ወደ አሞናውያን ለመሻገር ተነሣ።

11 የቃሬያ ልጅ ዮሐናና ከእርሱ ጋር የነበሩት የጦር መኰንኖች ሁሉ የናታንያ ልጅ እስማኤል የፈጸመውን ግፍ ሁሉ በሰሙ ጊዜ፣

12 የናታንያን ልጅ እስማኤልን ሊወጉ ሰዎቻቸውን ሁሉ ይዘው ሄዱ፤ በገባዖንም ባለው በታላቁ ኵሬ አጠገብ ደረሱበት።