ኤርምያስ 42:15-21 NASV

15 እንግዲህ የይሁዳ ቅሬታ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ወደ ግብፅ ለመሄድ ወስናችሁ እዚያ ለመቀመጥ ብትሄዱ፣

16 የፈራችሁት ሰይፍ በዚያ ያገኛችኋል፤ የሠጋችሁበት ራብ እስከ ግብፅ ድረስ ተከትሎአችሁ ይመጣል፤ በዚያም ትሞታላችሁ።

17 በዚያም ለመኖር ወደ ግብፅ ለመሄድ የወሰኑ ሁሉ በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር በእርግጥ ይሞታሉ፤ ከማመጣባቸውም ጥፋት አንድ እንኳ የሚተርፍ ወይም የሚያመልጥ አይገኝም።’

18 የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘ቍጣዬና መዓቴ በኢየሩሳሌም በሚኖሩት ሁሉ ላይ እንደ ፈሰሰ፣ እንዲሁ ወደ ግብፅ በገባችሁ ጊዜ መዓቴ በእናንተ ላይ ይፈሳል፤ እናንተም የመነቀፊያና የድንጋጤ፣ የመረገሚያና የመዘባበቻ ምልክት ትሆናላችሁ፤ ይህንም ስፍራ ዳግመኛ አታዩም።’

19 “እናንተ የይሁዳ ቅሬታ ሆይ፤ እግዚብሔር፤ ‘ወደ ግብፅ አትሂዱ’ ብሎአችኋል፤ እኔም ዛሬ እንዳስጠነቀቅኋችሁ በእርግጥ ዕወቁ፤

20 ‘ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን፤ እርሱ ያለህን ሁሉ ንገረን፤ እኛም እንታዘዛለን’ ብላችሁ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር በላካችሁኝ ጊዜ ሕይወታችሁን የሚያጠፋ ስሕተት ፈጸማችሁ።

21 እነሆ፤ ዛሬ በግልጥ ነገርኋችሁ፤ እናንተ ግን እግዚአብሔር አምላካችሁ ልኮኝ የነገርኋችሁን ሁሉ አሁንም አልታዘዛችሁም፤