1 በግብፅ ሰሜናዊ ክፍል በሚግዶል፣ በጣፍናስና በሜምፎስ እንዲሁም በግብፅ ደቡባዊ ክፍል ስለሚኖሩት የአይሁድ ሕዝብ እንዲህ የሚል ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ፤
2 “የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ላይ ያመጣሁትን ታላቅ ጥፋት አይታችኋል፤ ዛሬ ማንም የማይኖርባቸው ባድማ ሆነው ይታያሉ፤
3 ይህም የሆነው ስላደረጉት ክፋት ነው። እነርሱም ሆኑ እናንተ ወይም አባቶቻችሁ ላላወቋቸው ለሌሎች አማልክት በማጠንና በማምለክ አስቈጥተውኛል።
4 እኔም፣ ‘ይህን የምጠላውን አስጸያፊ ነገር አታድርጉ’ በማለት አገልጋዮቼን ነቢያትን ደጋግሜ ላክሁባቸው።
5 እነርሱ ግን አልሰሙም፤ ልብም አላሉም፤ ከክፋታቸው አልተመለሱም፤ ለሌሎችም አማልክት ማጠን አልተውም።
6 ስለዚህ መዓቴና ቍጣዬ ፈሰሰ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ላይ ነደደ፤ ዛሬ እንደሚታ ዩትም ማንም የማይኖርባቸው ፍርስራሾች አደረጋቸው።