ኤርምያስ 44:13-19 NASV

13 ኢየሩሳሌምን እንደቀጣሁ፣ በግብፅ የሚኖሩትን በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር እቀጣለሁ፤

14 ወደ ግብፅ የመጡት የይሁዳ ቅሬታዎች ወደ ይሁዳ ለመመለስ ቢመኙም ከጥቂት ስደተኞች በስተቀር አምልጦ ወይም ተርፎ ወደ ይሁዳ የሚመለስ አንድም ሰው አይኖርም።’ ”

15 ሚስቶቻቸው ለሌሎች አማልክት ማጠናቸውን ያወቁ ወንዶች ሁሉና በዚያ የነበሩት ሴቶች ሁሉ ይህም ማለት በሰሜንና በደቡብ ግብፅ የሚኖረው ሕዝብ ሁሉ ታላቅ ጉባኤ ሆነው ለኤርምያስ እንዲህ አሉት፤

16 “አንተ በእግዚአብሔር ስም የነገርኸንን መልእክት አንሰማም፤

17 እናደርጋለን ያልነውን ሁሉ እናደርጋለን፤ አባቶቻችን፣ ነገሥታታችንና ባለ ሥልጣኖቻችን በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች እንዳደረጉት ሁሉ እኛም ለሰማይዋ ንግሥት እናጥናለን፤ የመጠጥ ቍርባን እናፈስላታለን። በዚያን ጊዜ የተትረፈረፈ ምግብ ነበረን፤ በመልካም ሁኔታ እንገኝ ነበር እንጂ ምንም ክፉ ነገር አልገጠመንም።

18 ነገር ግን ለሰማይዋ ንግሥት ማጠንና የመጠጥ ቍርባን ማፍሰስ ከተውን ወዲህ፣ ሁሉን ነገር አጥተናል፤ በሰይፍና በራብም እያለቅን ነው።

19 ሴቶቹም፣ “ለሰማይዋ ንግሥት በምናጥንበትና የመጠጥ ቍርባን በምናፈስበት ጊዜ፣ በምስሏ ዕንጐቻ ስንጋግርና የመጠጥ ቍርባን ስናፈስላት ባሎቻችን አያውቁም ነበርን?” አሉ።