ኤርምያስ 44:2-8 NASV

2 “የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ላይ ያመጣሁትን ታላቅ ጥፋት አይታችኋል፤ ዛሬ ማንም የማይኖርባቸው ባድማ ሆነው ይታያሉ፤

3 ይህም የሆነው ስላደረጉት ክፋት ነው። እነርሱም ሆኑ እናንተ ወይም አባቶቻችሁ ላላወቋቸው ለሌሎች አማልክት በማጠንና በማምለክ አስቈጥተውኛል።

4 እኔም፣ ‘ይህን የምጠላውን አስጸያፊ ነገር አታድርጉ’ በማለት አገልጋዮቼን ነቢያትን ደጋግሜ ላክሁባቸው።

5 እነርሱ ግን አልሰሙም፤ ልብም አላሉም፤ ከክፋታቸው አልተመለሱም፤ ለሌሎችም አማልክት ማጠን አልተውም።

6 ስለዚህ መዓቴና ቍጣዬ ፈሰሰ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ላይ ነደደ፤ ዛሬ እንደሚታ ዩትም ማንም የማይኖርባቸው ፍርስራሾች አደረጋቸው።

7 “አሁንም የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ዘር እንዳይቀርላችሁ ወንዶችና ሴቶች፣ ልጆችና ሕፃናት በይሁዳ እንዳይገኙ ለምን እንዲህ ዐይነት ታላቅ ጥፋት በራሳችሁ ላይ ታመጣላችሁ?

8 ልትኖሩባት በመጣች ሁባት በግብፅ ምድር ለሌሎች አማልክት በማጠን፣ እጆቻችሁ ባበጇቸው ነገሮች ለምን ታስቈጡኛላችሁ? በምድር ባሉት ሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የርግማንና የመዘባበቻ ምልክት ለመሆን ራሳችሁን ታጠፋላችሁን?