ኤርምያስ 46:10-16 NASV

10 ያ ቀን ግን የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቀን ነው፤ጠላቶቹን የሚበቀልበት የበቀል ቀን።ሰይፍ እስኪጠግብ ድረስ ይበላል፤ጥማቱም እስኪረካ ድረስ ደም ይጠጣል።በሰሜን ምድር በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ፣የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር መሥዋዕት አዘጋጅቶአልና።

11 “ድንግሊቱ የግብፅ ሴት ልጅ ሆይ፤ወደ ገለዓድ ውጪ፤ የሚቀባ መድኀኒትም አምጪ፤ነገር ግን መድኀኒት የምታበዢው በከንቱ ነው፤ፈውስ አታገኚም።

12 ሕዝቦች ኀፍረትሽን ይሰማሉ፤ልቅሶሽም ምድርን ይሞላል።ጦረኛ በጦረኛው ይደናቀፋል፤ሁለቱም ተያይዘው ይወድቃሉ።”

13 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደናፆር መጥቶ ግብፅን እንደሚወጋ፣ እግዚአብሔር ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረው መልእክት ይህ ነው፤

14 “ይህን በግብፅ ተናገር፤ በሚግዶልም አሰማ፤በሜምፎስና በጣፍናስም እንዲህ ብለህ ዐውጅ፤በቦታችሁ ቁሙ፤ ተዘጋጁም፤በዙሪያችሁ ያሉትን ሰይፍ ይበላቸዋልና።

15 ጦረኞችህ ለምን ተዘረሩ? እግዚአብሔር ገፍትሮ ስለሚጥላቸው መቆም አይችሉም።

16 ደጋግመው ይሰናከላሉ፣አንዱም በሌላው ላይ ይወድቃል፤‘ተነሡ እንሂድ፤ወደ ሕዛባችንና ወደ ትውልድ አገራችን እንመለስ፤ከጠላትም ሰይፍ እናምልጥ’ ይላሉ።