ኤርምያስ 46:5-11 NASV

5 ነገር ግን ይህ የማየው ምንድ ነው?እጅግ ፈርተዋል፤ወደ ኋላ እያፈገፈጉ ነው፤ብርቱ ጦረኞቻቸው ተሸንፈዋል፤ዘወር ብለውም ሳያዩ፣በፍጥነት እየሸሹ ነው፤በየቦታውም ሽብር አለ፣”ይላል እግዚአብሔር።

6 “ፈጣኑ መሸሽ አይችልም፤ብርቱውም አያመልጥም፤በሰሜን በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ፣ተሰናክለው ወደቁ።

7 “ይህ እንደ ዐባይ ወንዝ ሙላት የሚዘለው፣እንደ ደራሽ ወንዝ የሚፈሰው ማነው?

8 ግብፅ እንደ ዐባይ ወንዝ ሙላት ይዘላል፤እንደ ደራሽ ወንዝ ይወረወራል፤‘እወጣለሁ፤ ምድርንም እሸፍናለሁ፤ከተሞችንና ነዋሪዎቻቸውን አጠፋለሁ’ ይላል።

9 ፈረሶች ሆይ ዘላችሁ ውጡ ሠረገሎችም ሸምጥጡ፤ጋሻ ያነገባችሁ የኢትዮጵያና የፉጥ ሰዎች፣ቀስት የገተራችሁ የሉድ ጀግኖች፣እናንተ ብርቱ ጦረኞች ተነሥታችሁ ዝመቱ።

10 ያ ቀን ግን የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቀን ነው፤ጠላቶቹን የሚበቀልበት የበቀል ቀን።ሰይፍ እስኪጠግብ ድረስ ይበላል፤ጥማቱም እስኪረካ ድረስ ደም ይጠጣል።በሰሜን ምድር በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ፣የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር መሥዋዕት አዘጋጅቶአልና።

11 “ድንግሊቱ የግብፅ ሴት ልጅ ሆይ፤ወደ ገለዓድ ውጪ፤ የሚቀባ መድኀኒትም አምጪ፤ነገር ግን መድኀኒት የምታበዢው በከንቱ ነው፤ፈውስ አታገኚም።