5 በዙሪያሽ ካሉት ሁሉ ዘንድ፣ሽብር አመጣብሻለሁ፤”ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤“እያንዳንዳችሁ ትሰደዳላችሁ፤በሽሽት ላይ ያሉትንም የሚሰበስብ አይገኝም።
6 “ከዚያ በኋላ ግን፣ የአሞናውያንን ምርኮ እመልሳለሁ፣”ይላል እግዚአብሔር።
7 ስለ ኤዶም፤የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ጥበብ ከቴማን ጠፍቶአልን?ምክር ከአስተዋዮች ርቆአልን?ጥበባቸውስ ተሟጧልን?
8 ዔሳውን በምቀጣ ጊዜ፣ጥፋት ስለማመጣበት፣እናንተ በድዳን የምትኖሩ ሆይ፤ወደ ኋላ ተመልሳችሁ ሽሹ፤ ጥልቅ ጒድጓድ ውስጥ ተደበቁ።
9 ወይን ለቃሚዎች ወዳንተ ቢመጡ፣ጥቂት ወይን አያስቀሩምን?ሌቦችስ በሌሊት ቢመጡ፣የሚሰርቁት የሚፈልጉትን ብቻ አይደለምን?
10 እኔ ግን ዔሳውን አራቍተዋለሁ፤መደበቅም እንዳይችል፣መሸሸጊያ ስፍራዎቹን እገልጣለሁ፤ልጆቹ፣ ዘመዶቹና ጎረቤቶቹ ይጠፋሉ፤እርሱም ራሱ አይኖርም።
11 ወላጆች የሌላቸውን ልጆችህን ተዋቸው፤ እኔ ለሕይወታቸው እጠነቀቃለሁ፤ መበለቶቻችሁም በእኔ ይታመኑ።”