ኤርምያስ 5:19-25 NASV

19 ሕዝቡ፣ ‘እግዚአብሔር አምላካችን ይህን ሁሉ ነገር ለምን አደረገብን?’ ብለው ቢጠይቁ ‘እኔን፣ እንደ ተዋችሁኝና በራሳችሁ ምድር ባዕዳን አማልክትን እንዳገለገላችሁ፣ እንደዚሁ የእናንተ ባልሆነ ምድር ባዕዳንን ታገለግላላችሁ’ ትላቸዋለህ።

20 “በያዕቆብ ቤት ይህን አሰሙ፣በይሁዳም እንዲህ ብላችሁ ዐውጁ፤

21 እናንት ዐይን እያላችሁ የማታዩ፣ጆሮ እያላችሁ የማትሰሙ፣ሞኞችና የማታስተውሉ ሰዎች ይህን ስሙ፤

22 ልትፈሩኝ አይገባችሁምን?” ይላል እግዚአብሔር፤“በእኔ ፊት ልትንቀጠቀጡስ አይገባምን?ለዘላለም ዐልፎት መሄድ እንዳይችል፣አሸዋን ለባሕር ድንበር አደረግሁ፤ማዕበሉ እየጋለበ ቢመጣ ከዚያ አያልፍም፤ሞገዱ ቢጮኽም ሊያቋርጠው አይችልም።

23 ይህ ሕዝብ ግን የሸፈተና እልከኛ ልብ አለው፤መንገድ ለቆ ሄዶአል፤

24 በልባቸውም፣‘የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ በጊዜው የሚያዘንበውን፣መከርን በወቅቱ የሚያመጣልንን፣አምላካችንን እግዚአብሔርን እንፍራ’ አላሉም።

25 በደላችሁ እነዚህን አስቀርቶባችኋል።ኀጢአታችሁ መልካሙን ነገር ከልክሎአችኋል።