ኤርምያስ 50:10-16 NASV

10 የባቢሎን ምድር ትዘረፋለች፤የሚዘርፏትም ሁሉ እስኪበቃቸው ይመዘብሩአታል፤”ይላል እግዚአብሔር።

11 “እናንተ ርስቴን የበዘበዛችሁ ሆይ፤ደስ ስላላችሁና ሐሤትም ስላደረጋችሁ፣በመስክ እንዳለች ጊደር ስለ ፈነጫችሁ፤እንደ ድንጒላ ፈረስ ስለ አሽካካችሁ፤

12 እናታችሁ እጅግ ታፍራለች፤የወለደቻችሁም ትዋረዳለች።እርሷም ምድረ በዳ፣ ደረቅ ምድርና በረሓ፣ከመንግሥታትም ሁሉ ያነሰች ትሆናለች።

13 ከእግዚአብሔር ቍጣ የተነሣ ባድማ ትሆናለች እንጂ፣የሚኖርባት አይገኝም፤በቍስሎችዋም ሁሉ ምክንያት፣በባቢሎን የሚያልፍ ሁሉ ይገረማል፤ ያፌዝባታልም።

14 “እናንተ ቀስት የምትገትሩ ሁሉ፣በባቢሎን ዙሪያ ተሰለፉ፤አንዳች ሳታስቀሩ ፍላጾችን ስደዱባት፤ በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአት ሠርታለችና።

15 ከየአቅጣጫው ጩኹባት፤እጇን ትሰጣለች፤ ምሽጓም ይወድቃል፤ቅጥሮቿ ይፈርሳሉ።ይህ የእግዚአብሔር በቀል ነውና፣እርሷን ተበቀሏት፤በሌሎቹ ላይ እንዳደረገችውም አድርጉባት።

16 ከባቢሎን ዘር የሚዘራውን፣በመከር ጊዜ ማጭድ የጨበጠውንም ዐጫጅ አጥፉት፤ከአጥፊው ሰይፍ የተነሣ፣እያንዳንዱ ወደ ገዛ ሕዝቡ ይመለስ፤ወደ ገዛ ምድሩም ይሽሽ።