6 በአራተኛው ወር በዘጠነኛው ቀን በከተማዪቱ ራብ ጸንቶ ስለ ነበር ሕዝቡ የሚበላውን አጣ፤
7 የከተማዪቱም ቅጥር ተነደለ፤ ሰራዊቱም ሁሉ ኰብልሎ ሄደ። ባቢሎናውያን በከተማዪቱ ዙሪያ ቢኖሩም፣ በንጉሡ የአትክልት ስፍራ አጠገብ በሁለት ቅጥሮች መካከል ባለው በር በሌሊት ከተማዪቱን ጥለው ሸሹ፤ ወደ ዓረባም አመሩ።
8 የባቢሎናውያንም ሰራዊት ንጉሥ ሴዴቅያስን ተከታትሎ በማሳደድ በኢያሪኮ ሜዳ ደረሱበት፤ ወታደሮቹም ሁሉ ከእርሱ ተለይተው ተበታትነው ሳለ፣ ንጉሡን ያዙት።
9 እርሱም በሐማት ምድር በሪብላ ወደ ነበረው ወደ ባቢሎንም ንጉሥ ተወሰደ፤ የባቢሎን ንጉሥ በዚያ ፈረደበት።
10 በሪብላም የባቢሎን ንጉሥ፣ የሴዴቅያስን ወንዶች ልጆች በአባታቸው ፊት ዐረዳቸው፤ የይሁዳንም ባለ ሥልጣኖች ሁሉ ገደላቸው፤
11 የሴዴቅያስንም ዐይኖች አወጣ፤ በናስ ሰንሰለትም አስሮ ወደ ባቢሎን ወሰደው፤ በዚያም እስከ ዕለተ ሞቱ በእስር ቤት አቈየው።
12 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በነገሠ በዐሥራ ዘጠነኛው ዓመት በአምስተኛው ወር፤ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን፣ የባቢሎን ንጉሥ ባለሟል የክብር ዘበኞች አዛዥ የነበረው ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።