ኤርምያስ 7:16-22 NASV

16 “እንግዲህ ስለማልሰማህ፣ ለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤ ልመና አታቅርብ፤ አትማጠን፤ አትማልድላቸውም።

17 እነርሱ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ላይ የሚያደርጉትን አታይምን?

18 ለሰማይዋ ንግሥት ቂጣ ሊጋግሩ፣ ልጆች እንጨት ይለቅማሉ፤ አባቶች እሳት ያቀጣጥላሉ፤ ሴቶችም ሊጥ ያቦካሉ፤ ሊያስቈጡኝም ለሌሎች አማልክት የመጠጥ ቍርባን ያቀርባሉ።

19 ለመሆኑ ይህን የሚያደርጉት እኔን ለማስቈጣት ነውን? ይላል እግዚአብሔር፤ “ይልቁን ይህን በማድረጋቸው በሚደርስባቸው ዕፍረት የሚጐዱት ራሳቸውን አይደለምን?

20 “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ቍጣዬና መዓቴ በዚህ ስፍራ በሰውና በእንስሳ ላይ፣ በዱር ዛፍና በምድር ፍሬ ላይ ይፈሳል፤ ይነዳል፤ አይጠፋምም።”

21 “ ‘የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የሚቃጠል መሥዋዕታችሁን በሌሎች መሥዋዕታችሁ ላይ ጨምሩ፤ ሥጋውንም ራሳችሁ ብሉ።

22 የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብፅ ባወጣኋቸው ጊዜ፣ ስለ መሥዋዕቶችና ስለሚቃጠል መሥዋዕት አልተናገርኋቸውም፤ ትእዛዝም አልሰጠኋቸውም።