2 “በእግዚአብሔር ቤት በር ቁም፤ በዚያም ይህን መልእክት ዐውጅ፤“ ‘እግዚአብሔርን ለማምለክ፣ በእነዚህ በሮች የምትገቡ የይሁዳ ሕዝብ ሁላችሁ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
3 የእስራኤል አምላክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “መንገዳችሁንና ሥራችሁን አስተካክሉ፤ እኔም በዚህ ስፍራ እንድትኖሩ አደርጋችኋለሁ።
4 ይህ ‘የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ’ ነው እያላችሁ በሐሰት ቃል አትታመኑ።
5 መንገዳችሁንና ሥራችሁን በእርግጥ ብታሳምሩ፣ በመካከላችሁ ቅንነት ቢኖር፣
6 መጻተኛውንና ድኻ አደጉን፣ መበለቲቱንም ባትጨቍኑ፣ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደም ባታፈሱ፣ የሚጐዷችሁን ሌሎች አማልክት ባትከተሉ፣
7 ለአባቶቻችሁ ለዘላለም ርስት አድርጌ በሰጠኋቸው ምድር፣ በዚህ ስፍራ አኖራችኋለሁ።
8 እናንተ ግን፣ ከንቱ በሆኑ የሐሰት ቃላት ታምናችኋል።”