15 ልብ ሁሉ ይቀልጥ ዘንድ፣የሚወድቁትም እንዲበዙ፣በበሮቻቸው ሁሉ፣የግድያውን ሰይፍ አኑሬአለሁ።ወዮ! እንዲያብረቀርቅ ተወልውሎአል፤ለመግደልም ተመዞአል።
16 ሰይፍ ሆይ፤ በስለትህ አቅጣጫ ሁሉ፣ወደ ቀኝም፣ወደ ግራም ቍረጥ።
17 እኔም በእጄ አጨበጭባለሁ፤ቍጣዬም ይበርዳል፤እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።”
18 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
19 “የሰው ልጅ ሆይ፤ የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ የሚመጣባቸውን የሁለት መንገዶች ካርታ ንደፍ፤ መንገዶቹም ከአንድ አገር የሚነሡ ናቸው፤ መንገዱ ወደ ከተማው በሚገነጠልበት ቦታ ላይ ምልክት አቁም።
20 በአሞናውያን ከተማ በረባት ላይ ለሚመጣው ሰይፍ አንደኛውን መንገድ ምልክት አድርግ፤ በይሁዳና በተመሸገችው ከተማ በኢየሩሳሌም ላይ ለሚመጣውም ሰይፍ ሁለተኛውን መንገድ ምልክት አድርግ።
21 የባቢሎን ንጉሥ በጥንቈላ ምሪት ለማግኘት በመንታ መንገድ ላይ በሁለቱ ጐዳናዎች መጋጠሚያ ላይ ይቆማል፤ ቀስቶቹን በመወዝወዝ ዕጣ ይጥላል፤ አማልክቱን ያማክራል፤ ጒበትንም ይመረምራል።