30 ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፣በምሬት ያለቅሱልሻል፤በራሳቸውም ላይ ዐቧራ ነስንሰው፣በዐመድ ላይ ይንከባለላሉ።
31 ስለ አንቺ ጠጒራቸውን ይላጫሉ፤ማቅም ይለብሳሉ፤በነፍስ ምሬት፣በመራራም ሐዘን ያለቅሱልሻል።
32 ስለ አንቺ በዋይታ ያለቅሳሉ፤እንዲህም እያሉ ሙሾ ያወርዳሉ፤“ባሕር ውጦት የቀረ፣እንደ ጢሮስ ማን አለ?”
33 ሸቀጥሽ ከባሕር በወጣ ጊዜ፤ብዙ ሕዝቦችን ታጠግቢ ነበር፣በታላቅ ሀብትሽና ሸቀጥሽ፣የምድርን ነገሥታት ታበለጽጊ ነበር።
34 አሁን ግን በጥልቅ ውሃ ውስጥ፣በባሕር ተንኰታኵተሻል፤ጭነትሽና ተሳፋሪዎችሽ ሁሉ፣ከአንቺ ጋር ሰጥመዋል።
35 በጠረፍ አገር የሚኖሩ ሁሉ፣በአንቺ ሁኔታ ተደናገጡ፤ንጉሦቻቸው በፍርሀት ራዱ፤ፊታቸውም ተለዋወጠ።
36 በሌሎች ሕዝቦች መካከል ያሉ ነጋዴዎች ምንኛ አፏጩብሽ!መጨረሻሽ አስደንጋጭ ሆነ፤ለዘላለምም አትገኚም።’ ”