18 ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፍ ተቀርጸውበት ነበር፤ የዘንባባ ዛፎቹ የተቀረጹት በኪሩብና በኪሩብ መካከል ነበር። እያንዳንዱም ኪሩብ ሁለት ፊት ነበረው፤
19 የሰው ፊት ያለው ኪሩብ በአንድ በኩል ወዳለው ዘንባባ የዞረ ሲሆን፣ የአንበሳ ፊት ያለውም በሌላ በኩል ወዳለው ዘንባባ ዞሮ ነበር። ሁሉም በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ላይ ተቀርጸው ነበር።
20 ከወለሉ አንሥቶ ከመግቢያው በላይ እስካለው ስፍራ ድረስ፣ የውስጡ መቅደስ የውጭ ግድግዳ ላይ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾአል።
21 የውስጡ መቅደስ በር መቃን ባለ አራት ማእዘን ነበር፤ ከቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት ለፊት ያለው በር እንዲሁ ባለ አራት ማእዘን ነበር።
22 ሦስት ክንድ ቁመት፣ ሁለት ክንድ ወርድ፣ ሁለት ክንድ ርዝመት ያለው የዕንጨት መሠዊያ ነበር፤ ማእዘኖቹ፣ መሠረቱና ጐኖቹ ሁሉ ከዕንጨት የተሠሩ ነበሩ። ሰውዬውም፣ “ይህች በእግዚአብሔር ፊት ያለች ገበታ ናት” አለኝ።
23 የውስጡ መቅደስና ቅድስተ ቅዱሳኑ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት በር አላቸው፤
24 እያንዳንዱ በር መካከሉ ላይ በመታጠፊያ የተያያዙ መዝጊያዎች አሉት።