1 ስለ ድርቅ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤
2 “ይሁዳ ታለቅሳለች፤ከተሞቿም ይማቅቃሉ፤በምድር ላይ ተቀምጠው ይቈዝማሉ፤ጩኸትም ከኢየሩሳሌም ወጥቶ ይሰማል።
3 መሳፍንት አገልጋዮቻቸውን ውሃ ፍለጋ ይሰዳሉ፤እነርሱ ወደ ውሃ ጒድጓዶች ይወርዳሉ፤ነገር ግን ውሃ አያገኙም፤ዐፍረውና ተስፋ ቈርጠው፣ራሳቸውን ተከናንበው፣ባዶ እንስራ ይዘው ይመለሳሉ።
4 በምድሪቱ ዝናብ ስለሌለ፣መሬቱ ተሰነጣጥቆአል፤ገበሬዎችም ዐፍረው፣ራሳቸውን ተከናንበዋል።
5 አንዳች ሣር ባለመኖሩ፣የሜዳ አጋዘን እንኳ፣እንደ ወለደች ግልገሏን ጥላ ትሄዳለች።