3 ምናልባትም ሰምተው እያንዳንዳቸው ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም ስላደረጉት ክፋት ላመጣባቸው ያሰብሁትን ቅጣት እተዋለሁ።
4 እንዲህም በላቸው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ባትሰሙኝና የሰጠኋችሁን ሕጌን ባትጠብቁ፣
5 ልትሰሟቸው ይገባ የነበረውን ወደ እናንተ ደጋግሜ የላክኋቸውን የአገልጋዮቼን የነቢያትን ቃል ባትሰሙ፣
6 ይህን ቤት እንደ ሴሎ አደርጋለሁ፤ ይህችንም ከተማ በምድር ሕዝብ ሁሉ ፊት የተረገመች አደርጋታለሁ።’ ”
7 ኤርምያስ ይህን ቃል በእግዚአብሔር ቤት ሲናገር፣ ካህናቱና ነቢያቱ፣ ሕዝቡም ሁሉ ሰሙ።
8 ነገር ግን ኤርምያስ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ሁሉ እንዲናገር ያዘዘውን ሁሉ ተናግሮ በጨረሰ ጊዜ፣ ካህናቱ፣ ነቢያቱና ሕዝቡም ሁሉ ይዘውት እንዲህ አሉ፤ “አንተ መገደል አለብህ!
9 ይህ ቤት እንደ ሴሎ ይሆናል፤ ይህቺም ከተማ ባድማና ወና ትሆናለች ብለህ በእግዚአብሔር ስም ለምን ትንቢት ትናገራለህ?” ’ ሕዝቡም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተሰብስበው ኤርምያስን ከበቡት።