ኤርምያስ 31:27-33 NASV

27 “እነሆ፤ የእስራኤልን ቤትና የይሁዳን ቤት” ይላል እግዚአብሔር፤ “በሰውና በእንስሳት ዘር የምሞላበት ጊዜ ይመጣል፤

28 ልነቅላቸውና ላፈርሳቸው፣ ልገለብጣቸውና ላጠፋቸው፣ መከራም ላመጣባቸው እንደ ተጋሁ ሁሉ፣ ላንጻቸውና ልተክላቸው ደግሞ እተጋለሁ” ይላል እግዚአብሔር።

29 “በዚያ ዘመን ሰዎች ዳግመኛ፣‘አባቶች በበሉት ጐምዛዛ የወይን ፍሬ፣የልጆች ጥርስ ጠረሰ’ የሚለውን ምሳሌ አይናገሩም።

30 ነገር ግን፣ እያንዳንዱ በገዛ ኀጢአቱ ይሞታል፤ ጐምዛዛ የወይን ፍሬ የሚበላ ሁሉ የራሱን ጥርስ ይጠርሳል።

31 “ከእስራኤል ቤትና፣ከይሁዳ ቤት ጋር” ይላል እግዚአብሔር፤“አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት፣ጊዜ ይመጣል።

32 ከግብፅ አወጣቸው ዘንድ፣እጃቸውን ይዤ በመራኋቸው ጊዜ፣ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ኪዳንአይደለም፤የእነርሱ ባልገ ሆኜ ሳለሁ፣ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋልና።”ይላል እግዚአብሔር።

33 “ነገር ግን ከዚያ ጊዜ በኋላ፣ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው” ይላል እግዚአብሔር፤“ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤በልባቸውም እጽፈዋለሁ።እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።