ኤርምያስ 32:30-36 NASV

30 “የእስራኤል ሕዝብና የይሁዳ ሕዝብ ከታናሽነታቸው ጀምሮ ከክፉ ነገር በቀር በፊቴ አንዳች በጎ ነገር አልሠሩም፤ በእርግጥም የእስራኤል ሕዝብ በእጃቸው ሥራ አስቈጡኝ፤ ይላል እግዚአብሔር።

31 ይህች ከተማ፣ ከተመሠረተችበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ከፊቴ እንዳስወግዳት ቍጣ ዬንና መዓቴን አነሣሥታለች፤

32 የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብዕጠ እነርሱ፣ ነገሥታታቸው፣ ባለሥልጣኖቻቸው፣ ካህናታቸው፣ ነቢያታቸው፣ የይሁዳ ሰዎችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ባደረጉት ክፋት ሁሉ አስቈጡኝ።

33 ፊታቸውን ሳይሆን ጀርባቸውን ሰጡኝ፤ ደጋግሜ ባስተምራቸውም አይሰሙም፤ ተግሣጽም አይቀበሉም።

34 ስሜ በተጠራበት ቤት አስጸያፊ ጣዖታቸውን አቆሙ፤ አረከሱትም።

35 ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለሞሎክ ይሠው ዘንድ በሄኖም ሸለቆ ለበኣል መስገጃ ኰረብቶችን ሠሩ፤ ነገር ግን ይሁዳን ኀጢአት ለማሠራት እንደዚህ ያለውን አስጸያፊ ተግባር እንዲፈጽሙ እኔ አላዘዝሁም፤ ከቶም አላሰብሁም።

36 “ ‘በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር ለባቢሎን ንጉሥ ዐልፋ ትሰጣለች’ ስላልሃት ስለዚህች ከተማ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤