ኤርምያስ 51:13-19 NASV

13 አንቺ በብዙ ውሃ አጠገብ የምትኖሪ፣በሀብትም የበለጸግሽ ሆይ፤የምትወገጂበት ጊዜ ወጥቶአል፤ፍጻሜሽ ደርሶአል።

14 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል በራሱ ምሎአል፤ብዛቱ እንደ አንበጣ መንጋ የሆነ ሰራዊት ያጥለቀልቅሻል፤እነርሱም በድል አድራጊነት በላይሽ ያቅራራሉ።

15 “ምድርን በኀይሉ የሠራ፣ዓለምን በጥበቡ የመሠረተ፣ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው።

16 ድምፁን ባንጐደጐደ ጊዜ በሰማይ ውሆች ይናወጣሉ፤ጉሙን ከምድር ዳርቻ ወደ ላይ እንዲወጣ ያደርገዋል፤መብረቅን ከዝናብ ጋር ይልካል፤ነፋስንም ከግምጃ ቤቱ ያወጣል።

17 “እያንዳንዱ ሰው ጅልና ዕውቀት የለሽ ነው፤የወርቅ አንጥረኛው ሁሉ በሠራው በጣዖቱ ዐፍሮአል፤የቀረጻቸው ምስሎቹ የሐሰት ናቸው፤እስትንፋስ የላቸውም።

18 እነርሱ ከንቱ የፌዝ ዕቃዎች ናቸው፣ፍርድ ሲመጣባቸው ይጠፋሉ።

19 የያዕቆብ ዕድል ፈንታ የሆነው ግን እንደ እነዚህ አይደለም፤እርሱ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ነውና፤እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነው።ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።