ሕዝቅኤል 11:1-7 NASV

1 መንፈስም ወደ ላይ አነሣኝ፤ ከዚያም በምሥራቅ በኩል ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት በር አመጣኝ። በበሩም መግቢያ ላይ ሃያ አምስት ሰዎች ነበሩ፤ በእነርሱም መካከል የሕዝቡን መሪዎች የዓዙርን ልጅ ያእዛንያንና የበናያስን ልጅ ፈላጥያንን አየሁ።

2 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ሰዎች ክፋትን የሚያቅዱና በዚህችም ከተማ ላይ ተንኰልን የሚመክሩ ናቸው።

3 እነርሱም፣ “ቤቶች የሚሠሩበት ጊዜ ቅርብ አይደለምን? ይህች ከተማ ድስት ናት፤ እኛም ሥጋ ነን’ ብለዋል።

4 ስለዚህ ትንቢት ተናገርባቸው፤ የሰው ልጅ ሆይ፤ ትንቢት ተናገር።”

5 የእግዚአብሔርም መንፈስ በላዬ ወረደ እንዲህም አለኝ፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የእስራኤል ቤት ሆይ፤ እናንተ እንዲህ ብላችኋል፤ እኔ ግን የልባችሁን ሐሳብ ዐውቃለሁ።

6 በዚህች ከተማ ብዙ ሰው ገድላችኋል፤ መንገዶቿንም ሬሳ በሬሳ አድርጋችኋል።’

7 “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በዚያ የጣላችኋቸው ሬሳዎች እነርሱ ሥጋ ናቸው፤ ይህችም ከተማ ድስት ናት፤ እናንተን ግን ከውስጧ አወጣችኋለሁ።