1 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ በዐመፀኛ ሕዝብ መካከል ተቀምጠሃል፤ የሚያዩበት ዐይን አላቸው፤ ነገር ግን አያዩም፤ የሚሰሙበትም ጆሮ አላቸው፤ ነገር ግን አይሰሙም፤ ዐመፀኛ ሕዝብ ናቸውና።
3 “ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፤ እነርሱ እያዩህ በቀን ጓዝህን ጠቅልለህ ለመሰደድ ተዘጋጅ፤ ካለህበትም ስፍራ ተነሥተህ ወደ ሌላ ቦታ ሂድ፤ ዐመፀኛ ቤት ቢሆኑም ምናልባት ይህን ያስተውሉታል።
4 በቀን እያዩ ጓዝህን እንደ ስደተኛ ጓዝ አውጣው፤ በምሽትም እያዩህ ስደተኛ እንደሚወጣ ውጣ።
5 እነርሱ እያዩ ግንቡን ነድለህ ጓዝህን በዚያ አሹልክ።
6 በፊታቸው ጓዝህን በትከሻህ ላይ አስቀምጥ፣ በምሽትም ተሸክመህ ውጣ። ለእስራኤል ቤት ምልክት አድርጌሃለሁና ምድሪቱን እንዳታይ ፊትህን ሸፍን።”