ሕዝቅኤል 13:15-21 NASV

15 መዓቴንም በቅጥሩና ኖራ በለሰኑት ሰዎች ላይ እሰዳለሁ፤ እናንተንም እንዲህ እላችኋለሁ፤ ‘ቅጥሩና ቅጥሩን በኖራ የለሰኑት የሉም፤

16 ኢየሩሳሌም ትንቢት የተናገሩላትና ሰላም ሳይኖር የሰላም ራእይ ያዩላት የእስራኤል ነቢያት ጠፍተዋል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

17 “አሁንም የሰው ልጅ ሆይ፤ ከራሳቸው አመንጭተው ትንቢት ወደሚናገሩ ወደ ሕዝብህ ሴቶች ልጆች ፊትህን መልስ፤ ትንቢትም ተናገርባቸው፤

18 እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የሕዝብን ነፍስ ለማጥመድ፣ ለአስማታቸው ለእጃቸው አንጓ ሁሉ አሸንክታብ ለሚያሰፉና፣ የተለያየ መጠን ያለውን የራስ መሸፈኛ ለሚያበጁ ሴቶች ወዮላቸው! በውኑ የሕዝቤን ነፍስ እያጠመዳችሁ የራሳችሁን ነፍስ ታድናላችሁን?

19 ዕፍኝ ለማይሞላ ገብስና ለቍራሽ እንጀራ ስትሉ ሐሰትን የሚያደምጥ ሕዝቤን እየዋሻችሁ መሞት የማይገባውን በመግደል፣ መኖር የማይገባውንም በማትረፍ በሕዝቤ መካከል አርክሳችሁኛል።

20 “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ የሕዝብን ነፍስ እንደ ወፍ በምታጠምዱበት አሸንክታብ ላይ ተነሥቻለሁ፤ ከክንዳችሁ ላይ እቀዳድደዋለሁ፤ እንደ ወፍ የምታጠምዱትንም ሕዝብ ነጻ አወጣዋለሁ።

21 መሸፈኛችሁን ቀድጄ ሕዝቤን ከእጃችሁ አድናለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ በቍጥጥራችሁ ሥር አይሆኑም፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።