2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለኢየሩሳሌም አስጸያፊ ተግባሯን ፊት ለፊት ንገራት፤
3 እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንዲህ ይላታል፤ ‘ዘርሽና ትውልድሽ ከከነዓን ምድር ነው፤ አባትሽ አሞራዊ፣ እናትሽም ኬጢያዊት ነበሩ።
4 በተወለድሽበት ቀን እትብትሽ አልተቈረጠም፤ ንጹሕ እንድትሆኚ በውሃ አልታጠብሽም፤ በጨው አልታሸሽም፤ በጨርቅም አልተጠቀለልሽም።
5 በርኅራኄ ዐይን ተመልክቶሽ ወይም አዝኖልሽ ከእነዚህ አንዱን እንኳ ያደረገልሽ ሰው አልነበረም፤ ይልቁንም በተወለድሽበት ቀን ተንቀሽ ስለ ነበር ሜዳ ላይ ተጣልሽ።
6 “ ‘እኔም በዚያ ሳልፍ፣ በደምሽ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ስትንፈራገጪ አየሁሽ፤ በደምሽም ውስጥ ተኝተሽ ሳለሽ፣ “በሕይወት ኑሪ!” አልሁሽ።
7 ሜዳ ላይ እንዳለ ቡቃያ አሳደግሁሽ፤ አንቺም አደግሽ፤ ብርቅ ዕንቍ ሆንሽ። ጡቶችሽ አጐጠጐጡ፤ ጠጒርሽም አደገ፤ ነገር ግን ከእናትሽ ማሕፀን እንደ ወጣሽ ዕርቃንሽን ነበርሽ።
8 “ዳግመኛም በአጠገብሽ በማልፍበት ጊዜ ወደ አንቺ ተመለከትሁ፤ ለመፈቀርም እንደ ደረስሽ ባየሁ ጊዜ፣ የመጐናጸፊያዬን ዘርፍ በላይሽ ዘርግቼ ዕርቃንሽን ሸፈንሁ። ማልሁልሽ፤ ከአንቺም ጋር ቃል ኪዳን ተጋባሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ አንቺም የእኔ ሆንሽ።