ሕዝቅኤል 16:4-10 NASV

4 በተወለድሽበት ቀን እትብትሽ አልተቈረጠም፤ ንጹሕ እንድትሆኚ በውሃ አልታጠብሽም፤ በጨው አልታሸሽም፤ በጨርቅም አልተጠቀለልሽም።

5 በርኅራኄ ዐይን ተመልክቶሽ ወይም አዝኖልሽ ከእነዚህ አንዱን እንኳ ያደረገልሽ ሰው አልነበረም፤ ይልቁንም በተወለድሽበት ቀን ተንቀሽ ስለ ነበር ሜዳ ላይ ተጣልሽ።

6 “ ‘እኔም በዚያ ሳልፍ፣ በደምሽ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ስትንፈራገጪ አየሁሽ፤ በደምሽም ውስጥ ተኝተሽ ሳለሽ፣ “በሕይወት ኑሪ!” አልሁሽ።

7 ሜዳ ላይ እንዳለ ቡቃያ አሳደግሁሽ፤ አንቺም አደግሽ፤ ብርቅ ዕንቍ ሆንሽ። ጡቶችሽ አጐጠጐጡ፤ ጠጒርሽም አደገ፤ ነገር ግን ከእናትሽ ማሕፀን እንደ ወጣሽ ዕርቃንሽን ነበርሽ።

8 “ዳግመኛም በአጠገብሽ በማልፍበት ጊዜ ወደ አንቺ ተመለከትሁ፤ ለመፈቀርም እንደ ደረስሽ ባየሁ ጊዜ፣ የመጐናጸፊያዬን ዘርፍ በላይሽ ዘርግቼ ዕርቃንሽን ሸፈንሁ። ማልሁልሽ፤ ከአንቺም ጋር ቃል ኪዳን ተጋባሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ አንቺም የእኔ ሆንሽ።

9 “በውሃ አጥቤ ከደም አጠራሁሽ፤ ዘይትም ቀባሁሽ።

10 ወርቀ ዘቦ አለበስሁሽ፤ ምርጥ ቈዳ ጫማም አደረግሁልሽ፤ ያማረ በፍታ አለበስሁሽ ውድ መደረቢያም አጐናጸፍሁሽ።