ሕዝቅኤል 16:43-49 NASV

43 “ ‘በእነዚህ ነገሮች አስቈጣሽኝ እንጂ የልጅነትሽን ወራት አላሰብሽም፤ ስለዚህ የሥራሽን እከፍልሻለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። በሌላው አስጸያፊ ተግባርሽ ሁሉ ላይ ዘማዊነትን አልጨመርሽምን?

44 “ ‘በምሳሌ የሚናገር ሁሉ፣ “ሴት ልጅ በእናቷ ትወጣለች” እያለ ይመስልብሻል።

45 አንቺ ባሏንና ልጆቿን የምትጸየፍ የእናትሽ ልጅ ነሽ፤ ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን የሚጸየፉ የእኅቶችሽ እኅት ነሽ። እናታችሁ ኬጢያዊት፣ አባታችሁም አሞራዊ ነበሩ።

46 ታላቂቱ እኅትሽ ከአንቺ በስተ ሰሜን ከሴት ልጆቿ ጋር የምትኖረው ሰማርያ ናት፤ ታናሺቱ እኅትሽም ከአንቺ በስተ ደቡብ ከሴት ልጆቿ ጋር የምትኖረው ሰዶም ናት።

47 አንቺም በእነርሱ መንገድ መሄድና አስጸያፊ ተግባራቸውን መከተል ብቻ ሳይሆን፣ ከእነርሱ ይልቅ ፈጥነሽ ምግባረ ብልሹ ሆንሽ።

48 እኔ ሕያው እግዚአብሔር! በራሴ እምላለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ አንቺና ሴት ልጆችሽ ያደረጋችሁትን እኅትሽ ሰዶምና ልጆቿ እንኳ አላደረጉትም።

49 “ ‘እነሆ የእኅትሽ የሰዶም ኀጢአት ይህ ነበር፤ እርሷና ሴት ልጆቿ እብሪተኞች፣ ጥጋበኞችና ደንታ ቢሶች ነበሩ፤ ድኾችንና ችግረኞችንም አይረዱም ነበር።