ሕዝቅኤል 16:52-58 NASV

52 እኅቶችሽን እንደ ጻድቃን በማስቈ ጠርሽ፣ ዕፍረትሽን ተከናነቢ፤ ኀጢአትሽ ከኀጢአታቸው የከፋ ስለ ሆነ፣ እነርሱ ከአንቺ ይልቅ ጻድቃን ሆኑ። እንግዲህ እኅቶችሽን ጻድቃን ስላስመሰልሻቸው፣ አንቺ ተዋረጂ፤ ዕፍረትሽንም ተከናነቢ።

53 “ ‘ነገር ግን የሰዶምንና የሴት ልጆቿን፣ እንዲሁም የሰማርያንና የሴት ልጆቿን ምርኮ እመልሳለሁ፤ የአንቺንም ምርኮ የእነርሱን በምመልስበት ጊዜ እመልሳለሁ።

54 ይህም የሚሆነው ለእነርሱ መጽናኛ በመሆንሽ እንድ ትዋረጂና ባደረግሽው ሁሉ እንድታፍሪ ነው።

55 እኅቶችሽ ሰዶምና ሴት ልጆቿ እንዲሁም ሰማርያና ሴት ልጆቿ ቀድሞ ወደነበሩበት ሁኔታ ይመለሳሉ፤ አንቺና ሴት ልጆችሽም ቀድሞ ወደ ነበራችሁበት ሁኔታ ትመለሳላችሁ።

56 በታበይሽበት ወቅት የእኅትሽን የሰዶምን ስም ለመጥራት እንኳ ፈቃደኛ አልነበርሽም፤

57 ይህም ኀጢአትሽ ከመገለጡ በፊት ነበር። አሁን ግን በዙሪያሽ ሆነው ለሚንቁሽ ለኤዶም ሴት ልጆችና ለጐረቤቶቿ ሁሉ፣ እንዲሁም ለፍልስጥኤም ሴት ልጆች መሣለቂያ ሆነሻል።

58 ለብልግናሽና ለአስጸያፊ ተግባርሽ የሚገባውን ቅጣት ትሸከሚያለሽ፤ ይላል እግዚአብሔር።