ሕዝቅኤል 17:15-21 NASV

15 ንጉሡ ግን በእርሱ ላይ ዐመፀ፤ ፈረሶችና ብዙ ሰራዊት ለማግኘት መልእክተኞችን ወደ ግብፅ ላከ፤ ይሳካለት ይሆን? እንዲህ ዐይነቱን ነገር የፈጸመ ያመልጣልን? ውል ያፈረሰስ ሳይቀጣ ይቀራልን?

16 “ ‘በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ልዑል እግዚአብሔር፤ መሐላውን ባቀለለበት፣ ውሉን ባፈረሰበት፣ በዙፋንም ላይ ባስቀመጠው ንጉሥ ምድር በባቢሎን ይሞታል።

17 በባቢሎናውያን ብዙ ሕይወት ለማጥፋት በከተማዋ ዙሪያ ዐፈር በሚደለድሉበትና ምሽግ በሚሠሩበት ጊዜ፣ ፈርዖን ከኀያል ሰራዊቱና ከብዙ ጭፍሮቹ ጋር በጦርነት ሊረዳው አይችልም።

18 ያደረገውን መሐላ በማቃለልና እጁን ያስገባበትን ውል በማፍረስ ይህን ሁሉ ስለ ፈጸመ ከቅጣት አያመልጥም።

19 “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በሕያውነቴ እምላለሁ ያቃለለውን መሐላዬንና ያፈረሰውን ኪዳኔን በራሱ ላይ አመጣለሁ።

20 መረቤን በላዩ እዘረጋለሁ፤ በወጥመዴም ይያዛል። ወደ ባቢሎን እወስደዋለሁ፤ በእኔ ላይ ስላመፀም በዚያ እፈርድበታለሁ።

21 የሚሸሸው ወታደሩ ሁሉ በሰይፍ ይወድቃል፤ የተረፉትም ወደ ነፋስ ይበተናሉ፤ እኔ እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ ታውቃላችሁ።