ሕዝቅኤል 17:3-9 NASV

3 እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ትልቅ ክንፍና ረጅም ማርገብገቢያ ያለው እንዲሁም አካሉ በላባ የተሸፈነ መልኩ ዥጒርጒር የሆነ ታላቅ ንስር ወደ ሊባኖስ መጥቶ የዝግባ ዛፍ ጫፍ ያዘ፤

4 ከጫፉም የላይኛውን ቀንበጥ ቀንጥቦ ወደ ነጋዴዎች ምድር ወሰደ፤ በሸቀጥ ነጋዴዎችም ከተማ ተከለው።

5 “ ‘ከዚህ በኋላ ከምድሪቱ ዘር ወስዶ በመልካም ዐፈር አኖረው፤ ውሃ እንደ ልብ ባለበት ቦታ አጠገብ እንደ አኻያ ዛፍ ተከለው፤

6 በበቀለም ጊዜ አጭርና ወደ ጐን የተንሰራፋ የወይን ተክል ሆነ፤ ቅርንጫፎቹም ወደ እርሱ አቅጣጫ ዐደጉ፤ ሥሮቹ ግን እዚያው ከበታቹ ቀሩ። ስለዚህ የወይን ተክል ሆነ፤ ቅርንጫፎችን አወጣ፤ ለምለም ቅጠሎችንም አበቀለ።

7 “ ‘ደግሞም ትልቅ ክንፍ ያለውና አካሉ በላባ የተሸፈነ ሌላ ታላቅ ንስር ነበር። ያ የወይን ተክልም ውሃ ለማግኘት ከተተከለበት ቦታ ሥሩን ወደ እርሱ ሰደደ፤ ቅርንጫፉንም ወደ እርሱ ዘረጋ።

8 ቅርንጫፍ እንዲያወጣ፣ ፍሬ እንዲያፈራና ያማረ የወይን ተክል እንዲሆን በአጠገቡ ብዙ ውሃ ባለበት በመልካም መሬት ተተክሎ ነበር።”

9 “እንዲህም በላቸው፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ያድግ ይሆን? ይጠወልግ ዘንድ ሥሩ ተነቅሎ ፍሬው አይረግፍምን? ቀንበጡም ሁሉ ይደርቃል። ከሥሩ ለመንቀል ብርቱ ክንድና የብዙ ሰው ጒልበት አያስፈልገውም።