6 በበቀለም ጊዜ አጭርና ወደ ጐን የተንሰራፋ የወይን ተክል ሆነ፤ ቅርንጫፎቹም ወደ እርሱ አቅጣጫ ዐደጉ፤ ሥሮቹ ግን እዚያው ከበታቹ ቀሩ። ስለዚህ የወይን ተክል ሆነ፤ ቅርንጫፎችን አወጣ፤ ለምለም ቅጠሎችንም አበቀለ።
7 “ ‘ደግሞም ትልቅ ክንፍ ያለውና አካሉ በላባ የተሸፈነ ሌላ ታላቅ ንስር ነበር። ያ የወይን ተክልም ውሃ ለማግኘት ከተተከለበት ቦታ ሥሩን ወደ እርሱ ሰደደ፤ ቅርንጫፉንም ወደ እርሱ ዘረጋ።
8 ቅርንጫፍ እንዲያወጣ፣ ፍሬ እንዲያፈራና ያማረ የወይን ተክል እንዲሆን በአጠገቡ ብዙ ውሃ ባለበት በመልካም መሬት ተተክሎ ነበር።”
9 “እንዲህም በላቸው፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ያድግ ይሆን? ይጠወልግ ዘንድ ሥሩ ተነቅሎ ፍሬው አይረግፍምን? ቀንበጡም ሁሉ ይደርቃል። ከሥሩ ለመንቀል ብርቱ ክንድና የብዙ ሰው ጒልበት አያስፈልገውም።
10 በሌላ ስፍራ ቢተከልስ ይጸድቅ ይሆን? የምሥራቅ ነፋስ ሲመታውስ ባደ ገበት ስፍራ ፈጽሞ አይደርቅምን?’ ”
11 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
12 “ለዚህ ዐመፀኛ ቤት እንዲህ በል፤ ‘የእነዚህ ነገሮች ትርጒም ምን እንደሆነ አታውቁምን?’ እንዲህ በላቸው፤ ‘የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፤ ንጉሥዋንና መሳፍንቷን ማረከ፤ ወደ ባቢሎንም ይዞአቸው ተመለሰ።