19 እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ ሥርዐቴን ተከተሉ፤ ሕጌንም ለመጠበቅ ትጉ።
20 በእኔና በእናንተ መካከል ምልክት ይሆን ዘንድ ሰንበቴን የተቀደሰ ቀን አድርጉት፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደሆንሁም ታውቃላችሁ።’
21 “ ‘ልጆቻቸው ግን በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ሰው ቢጠብቀው በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን አልተከተሉም፤ ሕጌን ለመጠበቅ አልተጉም፤ ሰንበቴንም አረከሱ። እኔም በምድረ በዳ መዓቴን አፈስባቸዋለሁ፤ ቍጣዬንም አወርድባቸዋለሁ ብዬ ነበር።
22 ነገር ግን ከግብፅ ሳወጣቸው ባዩ አሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ እጄን ሰበሰብሁ።
23 ደግሞም በአሕዛብ መካከል እንደምበትናቸውና ወደ ተለያዩ አገሮች እንደማፈልሳቸው በምድረ በዳ እጄን አንሥቼ በፊታቸው ማልሁ፤
24 ምክንያቱም ሥርዐቴን አቃለሉ፤ ሰንበቴን አረከሱ እንጂ ሕጌን አልጠበቁም፤ ዐይናቸውም ከአባቶቻቸው ጣዖታት ጋር ተጣብቆአል።
25 እኔም መልካም ላልሆነ ሥርዐትና በሕይወት ለማይኖሩበት ሕግ አሳልፌ ሰጠኋቸው፤