4 “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህን ለፍርድ ታቀርባቸዋለህን? በውኑ ለፍርድ ታቀርባቸዋለህን? የቀድሞ አባቶቻቸውን አስጸያፊ ተግባር ግለጽላቸው፤
5 እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እስራኤልን በመረጥሁበት ቀን፣ ለያዕቆብ ቤት ዘር እጄን አንሥቼ ማልሁላቸው፤ በግብፅም ራሴን ገለጥሁላቸው። እጄንም አንሥቼ፣ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ’ አልኋቸው።
6 በዚያን ቀን፣ ከግብፅ አውጥቻቸው ከምድር ሁሉ ይልቅ ውብ ወደሆነችው፣ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው፣ ወዳዘጋጀሁላቸውም ምድር እንደማስገባቸው ማልሁላቸው።’
7 እኔም፣ ‘እያንዳንዳችሁ ዐይኖቻችሁን ያሳረፋችሁባቸውን ርኩስ ምስሎች አስወግዱ፤ በግብፅ ጣዖታትም ራሳችሁን አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ’ አልኋቸው።
8 “ ‘እነርሱ ግን በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ሊሰሙኝም አልፈለጉም፤ ዐይኖቻቸውን ያሳረፉባቸውን ርኩስ ምስሎች አላስወገዱም፤ የግብፅንም ጣዖታት አልተዉም። እኔም በዚያው በግብፅ ምድር መዓቴን በላያቸው ላፈስ፣ ቍጣዬንም ላወርድባቸው ወስኜ ነበር።
9 ነገር ግን በመካከላቸው በኖሩባቸውና እስራኤልን ከግብፅ ምድር ለመታደግ ቃል ስገባ፣ በእነርሱ ዘንድ በተገለጥሁት በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ስለ ስሜ ክብር ተቈጠብሁ።
10 ስለዚህ ከግብፅ አውጥቼ ወደ ምድረ በዳ አመጣኋቸው።