12 በመካከልሽ ያሉ ሰዎች ደም ለማፍሰስ ጒቦ ይቀበላሉ፤ አንቺም ዐራጣና ከፍተኛ ወለድ በመውሰድ ከባልንጀራሽ የማይገባ ትርፍ ዘረፍሽ፤ እኔንም ረስተሻል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
13 “ ‘ያለ አግባብ ባገኘሽው ጥቅምና በመካከልሽ ባፈሰስሽው ደም ላይ እጄን አጨበጭባለሁ።
14 እኔ ልቀጣሽ በምነሣበት ጊዜ በልበ ሙሉነት መቆም ትችያለሽን? ወይስ እጅሽ ሊበረታ ይችላልን? እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ አደርገዋለሁም።
15 በሕዝቦች መካከል እበትንሻለሁ፤ በየአገሩም እዘራሻለሁ፤ ከርኵሰትሽም አጠራሻለሁ።
16 በሕዝቦች ዘንድ በምትረክሺበት ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቂያለሽ።’ ”
17 የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
18 “የሰው ልጅ ሆይ፤ የእስራኤል ቤት የብረት ዝቃጭ ሆነብኝ፤ ሁሉም በከውር ውስጥ ቀልጦ እንደሚቀር መዳብ፣ ቈርቈሮ፣ ብረትና እርሳስ ናቸው፤ እነዚህ ከብር የሚወጡ ዝቃጭ ናቸው።