ሕዝቅኤል 22:23-29 NASV

23 የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

24 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ምድሪቱን፣ ‘አንቺ ያልነጻሽ በቍጣም ቀን ዝናብ ያላገኘሽ ምድር ነሽ’ በላት።

25 መሳፍንቷ እያገሣ ግዳዩን እንደሚቦጫጭቅ አንበሳ በውስጧ ያሤራሉ፤ ሕዝቡን ይበላሉ፤ ንብረትንና የከበሩ ነገሮችን ይነጥቃሉ፤ ብዙዎችንም ሴቶች መበለት ያደርጋሉ።

26 ካህናቷ በሕጌ ላይ ያምፃሉ፤ ንዋያተ ቅድሳቴን ያረክሳሉ፤ የተቀደሰውን ከረከሰው አይለዩም፤ በጐደፈውና በንጹሑ መካከል ልዩነት እንደሌለ ያስተምራሉ፤ ሰንበታቴን ከማክበር ዘወር ብለዋል፤ በዚህም በመካከላቸው ተንቄአለሁ።

27 በውስጧ የሚገኙ መኳንንቷ ግዳይ እንደሚቦጫጭቁ ተኵላዎች ናቸው፤ በግፍ ትርፍ ለመሰብሰብ ደም ያፈሳሉ፤ ሕይወትም ያጠፋሉ።

28 ነቢያቷም በሐሰት ራእይና በውሸት ሟርት ይህን ሁሉ ድርጊት ያድበሰብሱላቸዋል፤ እግዚአብሔርም ሳይናገር፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ ይላሉ።

29 በምድሪቱ የሚኖረው ሕዝብ ይቀማል፤ ይዘርፋል፤ ፍትሕ በማጒደልም ድኻውንና ችግረኛውን ይጨቍናል፤ መጻተኛውንም ይበድላል።