1 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ከአንድ እናት የተወለዱ ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩ፤
3 ገና በወጣትነታቸው ዘማውያት በመሆን በግብፅ ሳሉ አመነዘሩ፤ በዚያችም ምድር አጐጠጐጤአቸው ተዳበሰ፤ የድንግልናቸውም ጒያ በእጅ ተሻሸ።
4 የታላቂቱ ስም ኦሖላ፣ የእኅቷም ኦሖሊባ ነበር፤ ሁለቱም የእኔ ሆኑ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ወለዱ። ስማቸውም፣ ኦሖላ ሰማርያ ናት፤ ኦሖሊባም ኢየሩሳሌም።
5 “ኦሖላ የእኔ ሆና ሳለ በእኔ ላይ አመነዘረች፤ ጦረኞች ከሆኑት ጎረቤቶቿ ከአሦራውያን ውሽሞቿ ጋር ሴሰነች፤
6 እነርሱም ሐምራዊ የለበሱ፣ ገዦችና አዛዦች፣ ሁሉም መልከ ቀና ጐበዛዝትና ፈጣን ፈረሰኞች ነበሩ።
7 እርሷ በዝሙት ራሷን ምርጥ ለሆኑት አሦራውያን ሁሉ አሳልፋ ሰጠች፤ አብረዋት ባመነዘሩት ሰዎች ጣዖት ሁሉ ረከሰች።