ሕዝቅኤል 23:17-23 NASV

17 ባቢሎናውያንም መጥተው ወደ ፍቅር መኝታዋ ገቡ፤ በፍትወታቸውም አረከሷት፤ እርሷም በእነርሱ ከረከሰች በኋላ ጠልታቸው ከእነርሱ ዘወር አለች።

18 ግልሙትናዋን በአደባባይ በፈጸመችና ዕርቃን በገለጠች ጊዜ ከእኅቷ ዘወር እንዳልሁ፣ ጠልቼአት ከእርሷም ዘወር አልሁ።

19 እርሷ ግን በግብፅ ያመነዘረችበት የወጣትነት ዘመኗ ትዝ እያላት የባሰ ዘማዊት ሆነች።

20 በዚያም አባለዘራቸው እንደ አህያ፣ የዘር ፍሰታቸውም እንደ ድንጒላ ፈረስ ዘር ፍሰት ከሆነ ውሽሞቿ ጋር አመነዘረች፤

21 በግብፅ ምድር ጒያሽን የታሸሽበትንና የወጣትነት ጡቶችሽን የተዳበስሽበትን የኰረዳነትሽን ብልግና ተመኘሽ።

22 “ስለዚህ፣ ኦሖሊባ ሆይ፤ ጌታእግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ጠልተሻቸው ከእነርሱ ዘወር ያልሽውን ውሽሞችሽን በአንቺ ላይ አስነሣለሁ፤ እነርሱንም ከየአቅጣጫው አመጣብሻለሁ፤

23 እነርሱም ባቢሎናውያንና ከለዳውያን ሁሉ፣ የፋቁድ፣ የሱሔና የቆዓ ሰዎች፣ ከእነርሱም ጋር አሦራውያን ሁሉ ናቸው። እነዚህም መልከ ቀና ጐበዛዝት ሲሆኑ፣ ሁላቸውም በፈረስ ላይ የተቀመጡ ገዦችና አዛዦች፣ የሠረገላ አዛዦችና ከፍተኛ ባለ ሥልጣኖች ነበሩ።