36 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ በኦሖላና በኦሖሊባ ትፈርዳለህን? እንግዲያውስ ጸያፍ ተግባራቸውን ንገራቸው።
37 አመንዝረዋል እጃቸውም በደም ተበክሎአልና። ከጣዖቶቻቸው ጋር አመነዘሩ፤ የወለዱልኝን ልጆቻቸውን እንኳ ለእነርሱ መብል ይሆኑ ዘንድ በእሳት ሠውተውላቸዋል።
38 ደግሞም ይህን አደረጉብኝ፤ በዚያኑ ቀን ቤተ መቅደሴን አረከሱ፤ ሰንበታቴንም አቃለሉ።
39 ልጆቻቸውን ለጣዖቶቻቸው በሠዉባት ዕለት ወደ መቅደሴ ገብተው አረከሷት፤ እንግዲህ በቤቴ ውስጥ ያደረጉት እንዲህ ያለውን ነው።
40 “ከዚህም በላይ ወንዶች ከሩቅ እንዲመጡላቸው መልእክተኛ ላኩ፤ እነርሱም መጡ። አንቺም ገላሽን ታጥበሽ፣ ዐይንሽን ተኵለሽና በጌጣጌጥ ተውበሽ ጠበቅሻቸው።
41 በተዋበ ዐልጋ ላይ ተቀመጥሽ፤ ዕጣኔንና ዘይቴን ያኖርሽበትንም ጠረጴዛ ከዐልጋው ፊት ለፊት አደረግሽ።
42 “የሚፈነጥዙ ሰዎች ድምፅ በዙሪያዋ ነበር፤ ከሚያውኩ ሰዎች ጋር ከበረሓ የመጡ ሰካራሞች ነበሩ፤ በሴትየዋና በእኅትዋም ላይ አንባር፣ በራሳቸውም ላይ የተዋበ አክሊል አደረጉላቸው።