ሕዝቅኤል 26:7-13 NASV

7 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘የነገሥታት ንጉሥ የሆነውን የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን ከፈረሶችና ከሠረገሎች ጋር፣ ከፈረሰኞችና ከታላቅ ሰራዊትም ጋር ከሰሜን በጢሮስ ላይ አመጣለሁ።

8 እርሱ መኻል አገር ያሉ ሰፈሮችሽን በሰይፍ ያወድማቸዋል፤ በዙሪያሽ ካብ ይክባል፤ እስከ ቅጥሮችሽ ጫፍ ድረስ ዐፈር ይደለድ ልብሻል፤ ጋሻውንም በአንቺ ላይ ያነሣል።

9 ግንብ መደርመሻውን በቅጥሮቿ ላይ ያነጣጥራል፤ በመሣሪያም ምሽጎችሽን ያፈርሳል።

10 ከፈረሶቹ ብዛት የተነሣ ዐቧራ ይሸፍንሻል፤ ሰዎች ቅጥሮችዋ ወደ ፈረሱ ከተማ እንደሚገቡ እርሱ በበሮችሽ በሚገባበት ጊዜ፣ ከፈረሶቹና ከጋሪዎቹ፣ ከሠረገሎቹም ድምፅ የተነሣ ቅጥሮችሽ ይናወጣሉ።

11 መንገዶችሽ ሁሉ በፈረሶቹ ኮቴ ይረጋገጣሉ፤ ሕዝብሽን በሰይፍ ይገድላል፤ ታላላቅ ምሰሶዎችሽ ወደ ምድር ይወድቃሉ።

12 ሀብትሽን ይዘርፋሉ፤ ሸቀጥሽን ይበዘብዛሉ፤ ቅጥሮችሽን ያፈርሳሉ፤ የተዋቡ ቤቶችሽን ያወድማሉ፤ ድንጋይሽን፣ዕንጨትሽንና የግንቦች ፍርስራሽ ወደ ባሕር ይጥላሉ።

13 ዘፈንሽን ጸጥ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህም የበገናሽ ድምፅ አይሰማም።