ሕዝቅኤል 27:11-17 NASV

11 የአራድና የሔሌክ ሰዎች፣ቅጥርሽን በየአቅጣጫው ጠበቁ፤የገማድ ሰዎችም፣ በምሽግሽ ውስጥ ነበሩ።ጋሻቸውንም በቅጥርሽ ዙሪያ ሰቀሉ፤ውበትሽንም ፍጹም አደረጉ።

12 “ ‘ከሀብትሽ ብዛት የተነሣ፣ ተርሴስ ከአንቺ ጋር የንግድ ልውውጥ ታደርግ ነበር፤ ብርና ብረት፣ ቈርቈሮና እርሳስ አምጥታ ሸቀጥሽን ትለውጥ ነበር።

13 “ ‘ያዋን፣ ቶቤልና ሞሳሕ ከአንቺ ጋር ይነግዱ ነበር፤ ባሪያዎችንና የናስ ዕቃዎችን በሸቀጥሽ ይለውጡ ነበር።

14 “ ‘የቤት ቴርጋማ ሰዎችም መጋዣዎችን፣ የጦር ፈረሶችንና በቅሎዎችን በሸቀጥሽ ለወጡ።

15 “ ‘የድዳን ሰዎች ከአንቺ ጋር ተገበያዩ፤ብዙ የጠረፍ አገሮችም የንግድ ደንበኞችሽ ነበሩ፤ በዝኆን ጥርስና በዞጲ ሸቀጥሽን ይገዙ ነበር።

16 “ ‘ምርትሽ ብዙ እንደ መሆኑ፣ ሶርያ ከአንቺ ጋር ትገበያይ ነበር፤ ሸቀጥሽንም በበሉር፣ በሐምራዊ ጨርቅ፣ በወርቀ ዘቦ፣ በጥሩ በፍታ፣ በዛጐልና በቀይ ዕንቍ ይለውጡ ነበር።

17 “ ‘ይሁዳና እስራኤል እንኳ ከአንቺ ጋር ተገበያይተዋል፤ የሚኒትን ስንዴ፣ ጣፋጭ ቂጣ፣ ማር፣ ዘይትና በለሳን በማምጣት በሸቀጥሽ ይለውጡ ነበር።