ሕዝቅኤል 3:16-22 NASV

16 ከሰባቱም ቀን በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤

17 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ቤት ጠባቂ አድርጌሃለሁ፤ ስለዚህ ቃሌን ስማ፤ የምነግርህንም ማስጠንቀቂያ አስተላልፍላቸው።

18 እኔ ኀጢአተኛውን ሰው፣ ‘በእርግጥ ትሞታለህ’ ባልሁት ጊዜ አንተ ባታስጠነቅቀው፣ ነፍሱንም ያድን ዘንድ ከክፉ ሥራው እንዲመለስ ባትነግረው፣ ያ ኀጢአተኛ በኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተንም ስለ ደሙ በኀላፊነት እጠይቅሃለሁ።

19 ነገር ግን ኀጢአተኛውን ሰው አስጠንቅቀኸው፣ ከኀጢአቱና ከክፉ መንገዱ ባይመለስ፣ እርሱ በኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ነፍስህን ታድናለህ።

20 “ጻድቁ ሰው ደግሞ ከጽድቁ ተመልሶ ኀጢአት ቢሠራ፣ እኔም መሰናክል በፊቱ ባስቀምጥ እርሱ ይሞታል፤ አንተ አላስጠነ ቀቅኸውምና በኀጢአቱ ይሞታል፤ ያደረገውም ጽድቅ አይታሰብለትም፤ አንተንም ስለ ደሙ በኀላፊነት እጠይቅሃለሁ።

21 ነገር ግን ጻድቁን ሰው ኀጢአት እንዳይሠራ ብታስጠነቅቀውና እርሱም ኀጢአትን ባይሠራ፣ ተጠንቅቆአልና በእርግጥ በሕይወት ይኖራል፤ አንተም ነፍስህን ታድናለህ።”

22 የእግዚአብሔር እጅ በላዬ ነበረ፤ እርሱም፣ “ተነሥተህ ወደ ረባዳው ስፍራ ሂድ፤ በዚያ እናገርሃለሁ” አለኝ።