ሕዝቅኤል 31:14-18 NASV

14 ስለዚህ በውሃ አጠገብ ያለ ማንኛውም ዛፍ፣ ጫፎቹን ችምችም ካለው ቅጠል በላይ ከፍ በማድረግ፣ ከእንግዲህ ራሱን በትዕቢት አያንጠራራም። ከእንግዲህ ውሃ በሚገባ ያገኘ ማንኛውም ዛፍ ወደዚህ ዐይነቱ ከፍታ አይደርስም። ሁሉም ከምድር በታች ወደ ጒድጓድ ከሚወርድ ሟች ጋር አብሮ እንዲሞት ተወስኖበታልና።”

15 “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ወደ መቃብር በወረደበት ቀን ጥልቅ ምንጮችን ስለ እርሱ በሐዘን ሸፈንኋቸው፤ ወንዞቹን ገታሁ፤ ታላላቅ ፈሳሾችም ተቋረጡ። በእርሱም ምክንያት ሊባኖስን ጨለማ አለበስሁ፤ የደን ዛፎችም ሁሉ ደረቁ።

16 ወደ ጒድጓድ ከሚሄዱት ጋር ወደ መቃብር ባወረድሁት ጊዜ ሲወድቅ በተሰማው ድምፅ አሕዛብ ደነገጡ። ከዚያም የዔድን ዛፎች ሁሉ፣ ምርጥና ልዩ የሆኑት የሊባኖስ ዛፎች፣ ውሃ የጠገቡትም ዛፎች ሁሉ ከምድር በታች ሆነው ተጽናኑ።

17 ከአሕዛብ መካከል ከእርሱ ጋር ያበሩ፣ በጥላው ሥር የኖሩ፣ በሰይፍ ከሞቱት ጋር ለመቀላቀል ወደ መቃብር ወርደዋል።”

18 “ ‘በዔድን ካሉት ዛፎች በውበትና በትልቅነት የሚወዳደርህ የትኛው ነው? ይሁን እንጂ አንተም እንደዚሁ ከዔድን ዛፎች ጋር ከመሬት በታች ትወርዳለህ፤ በሰይፍ ከተገደሉት፣ ካልተገረዙትም መካከል ትጋደማለህ።“ ‘እንግዲህ ፈርዖንና ስፍር ቍጥር የሌለው ሕዝቡ የሚደርስባቸው ይህ ነው፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”